ADDIS JAZZ FESTIVAL

አዲስ ጃዝ ፌስቲቫል በኢትዮጵያ እውቅ የሙዚቃና የኢቬንት ፕሮዳክሽን ድርጅቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ሙዚቃዊ የሚታወቅበት ዝግጅት ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛው የሆነው ፌስቲቫል አንጋፋና አዳዲስ ሙዚቀኞችን እንዲሁም የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ አርቲስቶች የሰሯቸውን አዳዲስ ስራዎች ያቀርባል፡፡ የፌስቲቫሉ የምረቃ ስነ ስርዓት በ2012 ዓ.ም የተደረገ ሲሆን አላማውም የጃዝ ሙዚቃን ለአዲስ አበባ ማስተዋወቅ፣አለም አቀፍ የጃዝ ሙዚቀኞች ጋር የትስስር እድልና መድረክ መፍጠር ነው፡፡በጃዝ አለም ውስጥ ከሚታወቁ በፌስቲቫሉ ላይ ከተሳተፉ እውቅ ሙዚቀኞች መካከል ሀይሉ መርጊያ፣አለማየሁ እሸቴ፣ሳሙዔል ይርጋ፣ክብሮም ብርሃኔ እና ቃየን ላብ ይገኙበታል፡፡ በዚህ አመት፤ ፌስቲቫሉ፤ በዩኔስኮ ዓለም አቀፍ የጃዝ ቀን ተብሎ ከተሰየመው ቀን ጋር በጋራ የሚካሄድ ሲሆን ቀኑም ጃዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰዎችን በማስተባበር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ሚና አጉልቶ ለማሳየት የሚያልም ነው፡፡

29 – 30 APRIL, 2023 • ADDIS ABABA, ETHIOPIA

29 – 30 APRIL, 2023
ADDIS ABABA, ETHIOPIA

ተሳታፊዎች

ዳዊት ይፍሩ

ዳዊት ይፍሩ ከ30 አመታት በላይ በዘለቀው የሙዚቃ ጉዞው በኢትዮጵያ የጃዝ ታሪክ ውስጥ ስመጥር ከሆኑ አቀናባሪዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ አንፋው ሙዚቀኛ ዳዊት ይፍሩ በሙዚቃ ውስጥ የፈጠረው ተጽእኖ እጅግ በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ በርካቶች መላው የኢትዮጵያን ዘመናዊ ሙዚቃን ቅርጽ/መልክ ሰጥቶታል እንዲሁም እንደ ሙሉቀን መለሰ፣ነዋይ ደበበና ኬኔዲ መንገሻ ያሉ እውቅ ድምጻውያንን የሙዚቃ ሞያን ፈር አስይዟል ይላሉ፡፡ ዳዊት ይፍሩ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የሙዚቃ ማኀበር ሊቀመንበርና አባል ሲሆን አሁንም ለጥበብና ለሙዚቃ ባለው ትጉህነት የአዲሱ ትውልድ ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኞችን እያበረታታ ይገኛል፡፡

Dawit-Yifru

ክለብ ኪለርስ

ክለብ ኪለርስ መነሻቸው ከስቶክሆልም ስዊድን የሆነ የሬጌ ባንድ ናቸው፡፡ በቀዳሚነት የስካና የሮክስቴዲ አፍቃሪዎች ሲሆኑ በቅርብ ጊዜ ግን ጀማይካዊ የሆኑ ማንኛውም የሙዚቃ ስልቶችን መደገፍ ጀምረዋል፡፡ የባንድ አባላቱ አና ማሪያ ኤስፒኖሳ (ድምጽ)፣ ዴዝመንድ ፎስተር (ጊታርና ድምጽ)፣ ፓትሪክ ኮላር (ኪይ ቦርድ)፣ አንደርስ ካፕሊን (ቤዝ)፣ቪክተር ብሮባክ (ትሮምቦን)፣ ጉስታቭ ቤንት (ሳክስ ፎን) እና ጉስታቭ ናለን (ድራም)፡፡

ጆርጋ መስፍን

ጆርጋ መስፍን ኢትዮጵያዊ ሳክስፎኒስት ሲሆን ውዳሴ የተሰኘው የኢትዮ ጃዝ ቡድን መስራች ነው፡፡ እራሱን በራሱ ያስተማረ ሙዚቀኛ ሲሆን ስራዎቹ ላይ የጃዝ መንፈስና ፈጠራ እንዲሁም ጥንታዊና ብዝኃነትን የተላበሱ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች አሻራቸውን አኑረዋል፡፡ ጆርጋ ለኃይሌ ገሪማ ጤዛ የተሰኘ ፊልም የማጀቢያ ሙዚቃን በመስራቱ የሚታወቅ ሲሆን ለዚህም በአምስተኛው ዱባይ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫልና በ22ኛው ካርቴጅ ፊልም ፌስቲቫል ላይ በምርጥ የሙዚቃ ምርጫና ምርጥ አቀናባሪ ዘርፍ ሽልማቶችን አሸንፏል፡፡

Ethiopian-Records

የኢትዮጵያ ልጅ

እንደገና ሙሉ/የኢትዮጵያ ልጅ በሙዚቃ ኢንዱስትሪው ውስጥ ላለፉት 18 ኣመታት የቆየ የሙዚቃ አቀናባሪ እና የቅጂ አርቲስት ሲሆን አዲስ የሆነውንና ኢትዮጵያዊ ቀለም ያለውን ኢትዮጵያዊ ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃን ለአድማጩ በማስተዋወቅ ፈር ቀዳጅ ነው። ባህላዊ የሙዚቃ ምቶች እና የድምፅ ቅንጅቶችን እንዲሁም የኤሌክትሮኒክ የሙዚቃ መሳሪያዎችን በመጠቀም ሁሌም ኢትዮጵያዊ እና አፍሪካዊ የሆነ ነገን የሚዳስሱ ሙዚቃዎቹን ይቀምራል። የኢትዮጵያ ልጅ አራት ኢፒ አልበሞችን (EPs) አሳትሟል።

ያንግ አዲስና ለታሪክ

ያንግ አዲስና ለታሪክ መቀመጫውን አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ያደረገ ባንድ ነው፡፡ ባንዱ ለባህላዊ ሙዚቃ እውቅና የሚሰጥ ሆኖ ጃዝን በአዲስ ውህደት ውስጥ የሚያይ ነው፡፡ ቡድኑ ዘጠኝ አባላቶችን አሉት፡፡

0R2A9279

ባልከው ዓለሙ

ባልከው ዓለሙ በ2014 ዓ.ም ፈልጌ የተሰኘው ገሚስ አልበሙን ለህዝብ ያደረሰ ሙዚቀኛ ነው፡፡ ከሙዚቃ ትዕይንቱ ጋር የመጀመሪያ ልምዱ የሚጀምረው በኢትዮጵያ አይድል የሙዚቃ ውድድር በ1997 ዓ.ም ና በ2004 ዓ.ም በተወዳደረ ጊዜ ነው፤በነዚህ ውድድሮች ውስጥ ምርጥ አምስት ውስጥ መግባት ችሏል፡፡ ሙዚቃው ዘመናዊ ኢትዮ ጃዝን ከምዕራብ አፍሪካ የሙዚቃ ምቶች ፅንሰ ሀሳብ ጋር ያዋሃደ የቀደምት አመታት ስሜት ያለው ነው፡፡የባልከው የሚስብ ድምጽና ጥልቅ ግጥሞች ገሚስ አልበሙን ዘመን የማይሽረው ያደርገዋል፡፡

ስንታየሁ በላይ

ስንታየሁ በላይ ከፍተኛ ተሰጥኦ ያላት ኢትዮጵያዊት ዘፋኝ ስትሆን የሙዚቃ ሞያዋን በ2015 ዓ.ም ፀደይ የተሰኘው ገሚስ አልበሟን በማውጣት ነው የጀመረችው፡፡ ድምጿ እንዲሁም ዘፈኗ ልዩ የሆኑና የሙዚቃ ቅንብሮቿ ስመጥር ከሆኑት አስቴር አወቀና ሀመልማል አባተ ጋር መወዳደር የሚችሉ ሲሆን የባህላዊ የአዝማሪ የአዘፋፈን ስልቶች አሻራም ድምጿ ላይ አርፎበታል፡፡ በክራርና በማሲንቆ መሳሪያዎች አጠቃቀሟ ላይ የምዕራብ አፍሪካ የሙዚቃ ባህሪያትን በማካተት ትታወቃለች፡፡

Anis

አኒስ ጋቢ

አኒስ ጋቢ ጥልቅ የሙዚቃ ፍቅር ያለው መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገ ሙዚቀኛ ነው፡፡ አኒስ ጋቢ “ሀደ ሚልኪ በተባለ ነጠላ ዜማው እውቅናን አግኝቷል፡፡ “ሀደ ሚልኪ” በኦሮሚያ ባህል ሥርዓት ውስጥ ሴቶች ያላቸውን ትልቅ ስፍራ የሚያሳይ ሲሆን አኒስ በዚህ ስራው በኦሮሚያ ባህል ዉስጥ የሴቶችን መብት እና የፍትህ ስርዓት የሆነውን ሲንቄን በሰፊው ለመዳሰስ ሞክሯል። አኒስ በአሁኑ ሰዓት የመጀመሪያ ገሚስ አልበሙን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

አዝማች

አዝማች መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የኢትዮ ሂፕ ሆፕ ቡድን ሲሆኑ ሶስት ሙዚቀኞችን ሰናይ፣ናኒና ልጅ ቴዲን አቅፏል፡፡ ቡድኑ የቀደምት ሂፕ ሆፕ/ራፕ እንዲሁም የኢትዮጵያ የሙዚቃ ምቶችና ዜማዎች ተጽእኖ በከፍተኛ ሁኔታ ያረፈበት መሆኑ ከሌሎች የሂፕ ሆፕ ቡድኖች የተለዩ ያደርጋቸዋል፡፡ የዘፈን ግጥማቸው ወጣቶችን ለማረበታታት አገር በቀል ታሪኮችን የሚናገሩ ናቸው፡፡ ቡድኑ በ2008 ዓ.ም ከተቋቋመ ጀምሮ እንደ ፕሮቶጄ (JAM) ማይክ ኤሊሰን (USA) ኤደን ደርሶ (ISR) ዳንኤል ለማ (SWE) እና AKALA (UK) ከተሰኙ ዓለም አቀፍ አርቲስቶች ጋር መድረክ ተጋርቷል፡፡ አዝማች በአሁኑ ሰዓት ከሙዚቃዊ ጋር ሁለት ገሚስ አልበሞችን የቀረፀ ሲሆን አልበሞቹም በያዝነው አመት ይለቀቃሉ፡፡

ጎንደር ፋሲለደስ

ጎንደር ፋሲለደስ በ1960ዎቹ የተመሰረተው አንጋፋው የቀድሞው ፋሲለደስ የባህል ቡድንን ፈለግ በመከተል እንደ አዲስ በየካቲት ወር 2007 ዓ.ም በ36 አባላት የተቋቋመ ነው።። ቡድኑን በማሰልጠን አንጋፋው እና እውቅ የሙዚቃ ባለሙያ የሆነው አርቲስት ሶፊ (ሱልጣን ኑሪ ሶፊ) አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ገና በምስረታ ላይ እያለ በ2007 ዓ.ም በአማራ ክልል የባህል ፌስቲቫል ላይ በተደረገ ውድድር 3ተኛ ደረጃ የወጣ ሲሆን እንደገናም በ2010 ዓም በተደረገ ክልል አቀፍ የባህል ሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ 1ኛ ደረጃ በመያዝ ወጥቷል ።በ2011 ዓም ሱዳን ሀገር በመሄድ የኢትዮጵያን የባህል ሙዚቃ ከ30,000 ሺ በላይ ለሚሆኑ ሱዳናዊያን እና የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ የባህል ሙዚቃ ስራዎችን አቅርቧል።

ፕሮግራም

ዕለት 1

ቅዳሜ, ሚያዚያ 21

8:00 ሰዓት
በር ይከፈታል
9:00 – 10:00 ሰዓት
ያንግ አዲስ እና ለታሪክ
10:30 – 11:30 ሰዓት
የሙዚቃዊ አርቲስቶች
12:00 -1:00 ሰዓት
ጆርጋ መስፍን
1:30 – 2:30 ሰዓት
ጎንደር ፋሲለደስ
3:00 ሰዓት
ክለብ ኪለርስ

ዕለት 2

እሁድ, ሚያዚያ 22 

8:00 ሰዓት
በር ይከፈታል
9:00 – 10:00 ሰዓት
የኢትዮጵያ ልጅ
10:30 – 11:30 ሰዓት
የሙዚቃዊ አርቲስቶች
12:00 – 1:00 ሰዓት
ዳዊት ይፍሩ
1:30 – 2:30 ሰዓት
ጎንደር ፋሲለደስ
3:00 ሰዓት
ክለብ ኪለርስ

For all general inquiries, please email info@addisjazzfestival.com

Scroll to Top